የማርበርግ ቫይረስ በሽታ

Share

Written by – Dr Kidstemariam Mesfin

በቅርቡ በሀገራችን በደቡብ ክልል በጂንካ ከተማ የተገኘው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ማርበርግ RNA በሚባል ቫይረስ የሚመጣና በወረርሽኝ መልክ የሚከሰት በሽታ ነው። ከኢቦላ ቫይረስ ጋር የአንድ ቤተሰብ አባል ነው። ሄሞሮጂክ  ፊቨርን ከሚያመጡ ቫይረሶች መካከልም አንዱ ነው።ይህ ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት የመተላለፍ አቅም አለው። ቫይረሱ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የታየ ቢሆንም በተከሰተበት ጊዜያት ግን እጅግ ከባድ የነበረ በሽታ ነው። ለመጀመርያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ 1967 በጀርመን እና በሰርቢያ ላብራቶሪ ውስጥ ተገኝትዋል። ይህ ቫይረስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአብዛኛው በአፍሪካ በዋሻ እና በማዕድን ቦታዎች ውስጥ በሚኖሩ የለሊት ወፎች ጋር ተያይዞ ተከስትዋል።

የማርበርግ ቫይረስ ምልክቶች ምልክቶች ምንድ ናቸው?

የ ማርበርግ ቫይረስ በሽታ ታማሚዎች ሁልጊዜ በሚባል ደረጃ ምልክቶችን ያሳያሉ። የማርበርግ  ቫይረስ የመጀመሪያ ምልክቶች እንደ ማንኛውም የቫይረስ ኢንፌክሽን  የተለመዱ እና ቀላል  ምልክቶች ናቸው።  ብዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አይገነዘቡም።  ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ በቫይረሱ ከተያዙ በ አማካኝ ከ2-21 ቀናት  ውስጥ ይጀምራሉ። ከነዚህም መካከል

  • ከፍተኛ እና በድንገት የሚጀምር ትኩሳት
  • እራስ ምታት
  • ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የሆድ ህመም
  • በጉንፋን የተዘጋ ጉሮሮ
  • የጡንቻ ህመም እና
  • ድካም ይገኙበታል

ይህ ደረጃ  ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ እየተባዛ እንደሆነ ያሳያል። በማርበርግ በሽታ ከተያዘ ወይም ከተጠረጠረ ሰው ጋር ከተገናኙ በኋላ እነዚህን ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ ማግኘት አስፈላጊ ነው።እነዚህን የመጀመሪያ ምልክቶች ተከትሎ በሽታው በጥቂት ቀናት (ከ5-13 ) ውስጥ በሰውነት ውስጥ  በመሰራጨት ከባድ እና አደገኛ ምልክቶችን ያሳያል። ከነዚህም ምልክቶች ውስጥ

  • በቆዳ ስር መድማት ወይም መበለዝ
  • የአፍንጫ እና የደድድ መድማት
  • እንዲሁም ደም የቀላቀለ ተውከት እና ተቅማጥ፣
  • ደም የቀላቀለ ሽንት
  • ደም የቀላቀለ አክታን
  • የጉበት ህመም፣
  • ከባድ የደም መርጋት እና የደም ግፊት መቀነስ ሊያሳይ ይችላል

ይህ የደም ስሮች  በቀላሉ የመድማት ሁኔታ በውስጣችን ያሉ አካሎቶቻችን ደም በአግባቡ እንዳይደርሳቸው እና ስራቸዉን በአግባቡ እንዳይሰሩ ያደርጋል። ይህ ደረጃ ለሕይወት አስጊ የሆኑ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። እስከ ሞት ሚያደርስ ጉዳትም ሊያስከትል ይችላል።  በጠንካራ የሕክምና ድጋፍ ለታካሚዎች በተናጥል እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል። ሕክምናውን ቀደም ብሎ መጀመር የማገገም እድሉን የተሻለ ያደርገዋል።  በዚህ በሽታ ከተያዙ የመሞት እድል ከ 10 ፐርሰንት እስከ 90 ፐርሰንት ይደርሳል።

የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች

የበሽታው ዋነኛ መተላለፊያ መንገድ በበሽታው ከተያዘ ሰው የሚወጡ ማንኛውም አይነት ፈሳሽ ጋር የሚኖር ቀጥተኛ ንክኪ ነው። እነዚ የሰውነት ፈሳሾች ወደ ሰው አካል ውስጥ ከገቡ በኋላ ቫይረሱን በፍጥነት ሊያሰራጩ ይችላሉ። ከነዚህም መካከል ደም፣ እምባ፣ ላብ ፣ሽንት ፣ተውከት ተጠቃሽ ናቸው።

በበሽታው የተያዘ ሰው የነካቸውን ቦታዎች እና የተጠቀማቸውን እቃዎች (አንሶላ ፣ ፎጣ፣ ልብሶች…)  በመንካት ይተላለፋል። በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ወይም እንስሳት ጋር በቀጥታ በመገናኘትም ይተላለፋል። በተጨማሪም በበሽታው ህይወቱ ያለፈ ሰው ሰውነት ጋር የሚኖር ንክኪም ቫይረሱን ማስተላለፍያ አመንገድ ነው።

የማርበርግ ቫይረስ በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ማርበርግ ቫይረስ  በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ስንከባከብ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እና የእጅ ጓንት መጠቀም ፣እጅን በሳኒታይዘር ማፅዳት ወይም በሳሙና እና በውሃ በደንብ መታጠብ፣  ከተያዘ ሰው ጋር ቅርበት አለመፍጠር ፣ ቫይረሱ አንዳይተላለፍ መከላከያ መንገድ ነው። በበሽታው ህይወቱ ያለፈ ሰውን በምገንዝበት አና በሚቀበርበት ሂደትም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ህክምና

ሀኪሞች ቫይረሱ አንዳለበት የተጠረጠረ ሰው በሚያገኙ ጊዜ ታካሚውን ለብቻው በመለየት እና ምርመራ በማረግ ህክምናውን ይጀምራሉ። የማርበርግ ሄሞሮጂክ ፊቨር በሽታ ምልክቶች ከሌሎች  እንደ ማላሪያ ወይም ታይፎይድ ያሉ በሽታዎች ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ፣ ይህ በሽታ ከእነዚህ በተለየ መለየት ያስፈልጋል። በሽታው ማርበርግ ቫይረስ እንደሆነ ለማረጋገጥ ዶክተሮች ልዩ  የላብራቶሪ ምርመራዎችን ማድረግ አለባቸው።

ይህ በሽታ የታወቀ ምንም አይነት ህክምና ወይም የመከላከያ ክትባት ባይኖርም ዋናው በሽታውን የመቆጣጠሪያ መንገድ በሽታውን መከላከል ነው። የቫይረሱ ምልክቶችን በሚያሳዩ በጊዜ ወይም የበሽታው ምልክት ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ካለ ቶሎ ወደ ህክምና መስጫ  ተቋማት መሄድ ቶሎ የህክምና አርዳታ ለማግኘት እንዲሁም በሽታውን ላለማስተላለፍ ወሳኝ ነው። በቤት ውስጥ ማከም የሚችሉት ነገር ስላልሆነም የሆስፒታል እንክብካቤ ያስፈልገዋል።

ለበለጠ መረጃ

Dr. Kidstemariam Mesfin is a General Practitioner who graduated from Jimma University. At Med In Ethiopia, she contributes to the development of medical resources for both healthcare professionals and the general public, focusing on creating reliable, engaging content that simplifies complex healthcare topics and supports professional development across Ethiopia’s health community.

1 thought on “የማርበርግ ቫይረስ በሽታ”

  1. ዶ/ር ቅድስተማርያም ለሰጠሽን ጥልቅ እውቀት እናመሰግናለን። ወደፊትም ካንቺ ብዙ እንጠብቃለን።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You cannot copy content of this page

Scroll to Top