የስኳር በሽታ መንስኤ ምልክቶች ምርመራ እና ሕክምና

Share

Written by – Dr Michael Mengesha

 

የስኳር በሽታ መንስኤ፣ ምልክቶች፣ ምርመራ እና ሕክምና

የስኳር በሽታ ምንድነው?  

የስኳር በሽታ ሰውነት ስኳር የሚጠቀምበትን መንገድ የሚያስተጓጉል በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ የሚድን በበሽታ ሳይሆን ዕድሜ ልክ የሚቆይ የበሽታ ዓይነት ነው፡፡ በጥንቃቄ ካልተያዘ ለተጨማሪ የአካል ጉዳት ብሎም ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡

በሰውነት ውስጥ ያሉት ሁሉም ሕዋሳት በትክክል እንዲሰሩ ስኳር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ኢንሱሊን ደግሞ ሰውነታችን ስኳርን እንዲወስድ እና እንዲጠቀም፣ ስብ እንዲከማች እና ፕሮቲን እንዲገነባ የሚረዳ ሆርሞን ነው፡፡ 

በሰውነታን ውስጥ በቂ ኢንሱሊን ከሌለ ወይም ደግሞ ሰውታችን ለኢንሱሊን ምላሽ መስጠቱን ከአቆመ ስኳር በደም ውስጥ ይከማቻል፡፡  ይህም የስኳር በሽታ ያመጣል፡፡

 የስኳር በሽታ ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡

 • ዓይነት 1 (Type 1) የስኳር በሽታ 

ዓይነት 1 የስኳር በሽታ ዋነኛ ችግሩ ቆሽት በቂ ኢንሱሊን አለማምረቱ ነው፡፡ ይህ የስኳር በሽታ ዓይነት ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በልጅነት ወይም በወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው፡፡  በአጠቃላይ የስኳር በሽታ ከአለባቸው ሰዎች ከ 5 እስከ 10 በመቶ የሚሆኑት በዚህ የስኳር በሽታ ዓይነት ይይዛሉ፡፡

 • ዓይነት 2 (Type 2) የስኳር በሽታ

በዓይነት 2 የስኳር በሽታ ችግሩ የሰውነት ሴሎች ለኢንሱሊን ምላሽ አለመስጠታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ሰውነት በቂ ኢንሱሊን አያመርትም፡፡ ከአጠቃላይ የስኳር በሽታ ከአለባቸው ሰዎች 90 በመቶ የሚሆኑት በ ታይፕ 2 የስኳር በሽታ ይይዛሉ፡፡

በእርግዝና  ጊዜ የስኳር በሽታ ሊከሠት ይችላል?

ነፍሰ ጡር ሴቶች (በግምት ከ 3 እስከ 5 በመቶ) በእርግዝና ወቅት በስኳር በሽታ ይይዛሉ፡፡  የእርግዝና የስኳር በሽታ ከ 2ኛ ዓይነት የስኳር በሽታ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ 2ኛው ዓይነት የስኳር በሽታ አይቀጥልም፡፡  አልፎ አልፎ ግን በእርግዝና ወቅት የስኳር በሽታ ያለባቸው ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ለታይፕ 2 የስኳር በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ 

የስኳር በሽታ ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

 • ከፍተኛ ውኃ ጥም
 • ድካም
 • በብዛት ሽንት መሽናት
 • ክብደት መቀነስ

የስኳር በሽታ መኖሩን እንዴት ማወቅ ይቻላል?  

አንድ ሰው ከሚከተሉት መስፈርቶች ውስጥ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ምልክቶች ከአለው የስኳር ሕመምተኛ ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡

 • በቀን ውስጥ በማንኛውም ሰዓት በደም ውስጥ የአለው የስኳር መጠን ተለክቶ (Random Blood Sugar)

የደም የስኳር መጠን 200 mg / dL (11.1 mmol / L) ወይም ከዚያ በላይ ከሆነና የሚከተሉት የስኳር በሽታ ምልክቶች ከታዮ (ብዙ ዉሃ መጠጣት፣ ብዙ ምግብ መመገብና ብዙ ሽንት መሽናት)

 • ከ 6 – 8 ሰዓት ፆም በኋላ የደም ውስጥ የስኳር መጠን ሲለካ (Fasting Blood Sugar)

የደም የስኳር መጠን 126 mg / dL (7.0 mmol / L) ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ

 • የ 3 ወር አማካኝ የስኳር መጠን ፐርሰንታይል (ሂሞግሎቢን ኤ 1 ሲ /HgA1c/) ምርመራ 6.5 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ። 

የስኳር በሽታን ለማረጋገጥ የደም የስኳር መጠን ልኬትን ሁለቴ ወይም ከሁለት ጊዜ በላይ ተሠርቶ መረጋገጥ አለበት። 

 

 

ከስኳር ሕመም ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ምን ምንድን ናቸው?

በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከፍ ካለ በጊዜ ሂደት ከባድ ችግሮች ያስከትላል፡፡  ለምሳሌ፡-

 • የነርቭ በሽታ
 • የኩላሊት በሽታ
 • የማየት ችግር (አልፎ ተርፎም ዓይነ ስውርነት)
 • በእጅ እና በእግር ላይ ስሜት ማጣት፤ ይህም ለቁስለት ያጋልጣል፡፡
 • የልብ ሕመም እና የደም ቧንቧ መጥበብ፤ የስኳር በሽታ የአለባቸው ሰዎች የስኳር በሽታ ከሌላቸው ሰዎች ይልቅ በልብ በሽታ እና በስትሮክ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡  የደም ግፊትን እና ኮሌስትሮልን ዝቅተኛ ማድረጉ እነዚህን አደጋዎች ለመቀነስ ይረዳል፡፡
 • በሽታ የመከላከል ዐቅም ማነስ እና ለኢንፌክሽን መጋለጥ፤

 በደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ዝቅተኛ መሆኑም ችግር ያስከትላል፡፡  ልብ በፍጥነት መምታት፣ መንቀጥቀጥ  እና ላብ ላብ ማለት ይኖራል።  በዚህ ጊዜ እንደ ከረሜላ ያሉ ጣፋጭነት ያላቸውን ምግቦችን ቶሎ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

የስኳር በሽታ እንዴት ይታከማል?

በዋነኝነት ሦስት መንገዶች አሉ፡፡ 

 • የአመጋገብ ለውጥ
 • የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ
 •  በሐኪም የታዘዙ መድኃኒቶች

የአመጋገብ ለውጥ ፡- የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ምን እንደሚበሉ ማቀድ አለባቸው፡፡

 • ካርቦሃይድሬት – ከፍተኛ ካርቦሃይድሬት የአላቸው ለሰውነታችን ኃይል ሰጪ   ምግቦች የሰውን የደም ውስጥ ስኳር መጠን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ የምግብ ዓይነቶች ናቸው፡፡  ለስኳር ሕመምተኞች ካርቦሃይድሬትን ከፍራፍሬዎች እና ከአትክልቶች ማግኘት በጣም ጥሩ ነው፡፡
 • ፕሮቲን – ለስላሳ ቀይ ሥጋ፣ ዓሣ፣ እንቁላል፣ ባቄላ፣ አተር፣ አኩሪ አተር ምርቶች፣ ለውዝ እና ጥራጥሬዎችን መመገብ ተመራጭ ነው፡፡ በተጨማሪም ሐኪምዎ በየቀኑ ምን ያህል የፕሮቲን መጠን የአለው ምግብ መመገብ እንዳለብዎ ይነግርዎታል።  
 • ስብ – ዓሣ፣ አቮካዶ፣ የወይራ ዘይትና ለውዝ 
 • ካሎሪ –   ከመጠን በላይ ክብደት የአላቸው እና ክብደታቸውን መቀነስ የሚፈልጉ ሰዎች በየቀኑ አነስተኛ የካሎሪ መጠን የአላቸውን ምቦች መመገብ አለባቸው፡፡ 
 • ፋይበር – ብዙ ፋይበር ያላቸውን ምግቦች መመገብ የሰውን የደም ስኳር መጠን ለመቆጣጠር ይረዳል፡፡
 • ጨው – የደም ግፊት የአለባቸው ሰዎች ብዙ ጨው የያዙ ምግቦችን መመገብ የለባቸውም፡፡  ከፍተኛ የደም ግፊት ያላቸው ሰዎችም እንደ ፍራፍሬ፣ አትክልቶች፣ አነስተኛ ቅባት ያላቸውን የወተት ተዋጽዖዎች እና ጤናማ ምግቦችን መመገብ አለባቸው፡፡
 • አልኮል – በቀን ከ 1 በላይ መጠጥ (ለሴቶች) ወይም 2 መጠጦች (ለወንዶች) መጠጣት  በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ከፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ እንዲሁም በውስጣቸው የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ሶዳ ያላቸው መጠጦች በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ለስኳር ህመምተኞች የተከለከሉ እና የሚፈቀዱ የምግብ አይነቶች ዝርዝር ይህን በመጫን ማውረድ ይችላሉ።

የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ – በሳምንት ከ 3 – 5 ጊዜ ከ 30 – 60 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፡፡

 በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶች 

 – በመርፌ የሚሰጡ የኢንሱሊን ዓይነቶች

 – የሚዋጡ የኪኒን መድኃኒቶች – ለምሳሌ ሜቲፎርሚን፣ ዳዎኒልና ሌሎችም 

ዓይነት 1 የስኳር በሽታ እንዴት ይታከማል?

 • ዓይነት 1 የስኳር በሽታ መደበኛ የደም ስኳር ቁጥጥር እና በኢንሱሊን ሕክምናን ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም አመጋገብን ማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ዓይነት 2 የስኳር በሽታ እንዴት ይታከማል?

 • አመጋገብን ከማስተካከል እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ በተጨማሪ የደም ስኳርን ለመቆጣጠር የሚረዱ  መድኃኒቶች አሉ፡፡አብዛኛውን ጊዜ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች የሚወስዱት የመጀመሪያው መድኃኒት ሜቲፎርኒን የተባለ ክኒን ነው፡፡  አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰውነት ብዙ ኢንሱሊን እንዲያመርት ወይም ኢንሱሊን ሥራውን እንዲሠራ የሚያግዙ ክኒኖችን መውሰድ ያስፈልጋቸዋል፡፡  ሌሎች ደግሞ የኢንሱሊን መርፌ ይፈልጋሉ፡፡ የ ዓይነት 2 የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎችም በበሽታው ምክንያት የሚከሠቱትን ችግሮች ለመቀነስ መድኃኒቶችን መውስድ ያስፈልጋቸዋል፡፡  ለምሳሌ የደም ግፊትን ለመቀነስ የሚያገለግሉ መድኃኒቶች በተጨማሪም በልብ ድካም የመያዝ ዕድልን የሚቀንሱ ኪኒኖች ሊያስፈልጉ ይችላሉ፡፡

አንድ የስኳር ሕመምተኛ ትክክል የሆነ የሕክምና ዕቅድ ለማዘጋጀት ከሐኪሙ ወይም ከነርስ  ጋር እየተነጋገሩ አብረው እንዲሠሩ ይመከራል። ከዚህ በተጨማሪ በደም ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በየጊዜው መለካት እና ከፍ ያለ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ 

እነዚህ መድኃኒቶች አንዳንዴም የስኳር መጠንን በጣም ዝቅ ስለሚያረጉ፤ እንደ ማዞር፣ ላብ ላብ ማለት፣ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ራስን መሳት እና ሞት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ከሐኪም ጋር በቅርበት መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡

የስኳር ሕክምና ግቦች ምንድናቸው?  

 – የደም ስኳር በተገቢው ደረጃ እንዲደርስ ማድረግ፤

 – ለወደፊቱ ሊከሠቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን መከላከል፤

 የስኳር በሽታን መከላከል ይቻላል?  

አዎ ይቻላል፡፡

በስኳር በሽታ የመያዝ ዕድልን ለመቀነስ ማድረግ የሚችሉት በጣም አስፈላጊው ነገር፤ ክብደትዎን መቆጣጠር እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ነው፡፡

የሕክምና ክትትሉ ውጤታማ መሆኑ በምን ይታወቃል?  

ሕክምናው በትክክል እየሠራና ውጤታማ መሆኑን ለማወቅ፤ አንዱ መንገድ የደምን የስኳር መጠን መመርመር ነው፡፡  

በተጨማሪ ሐኪሙ “HgA1c” የተባለ የደም ምርመራ ያደርጋል፡፡  በዚህ ምርመራ ባለፉት 2 እና 3 ወሮች ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ምን ያህል እንደሆነ ይፈተሻል፡፡

በሐኪም የታዘዘው መድኃኒት ኪኒን እየተወሰደ በደም ውስጥ የአለው የስኳር መጠን ከፍ ያለ ወይም የማይቀንስ ከሆነ፤  

 ከ 2 እስከ 3 ወራቶች ኪኒን ከተወሰደ በኋላ የደም ውስጥ የስኳር መጠን አሁንም ከተለመደው ከፍ ያለ ከሆነ ሀኪሙ ሁለተኛ መድኃኒት ሊጨምር ይችላል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You cannot copy content of this page